የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የሰፈር እድር ፤ መስከረም 30 እና መለዮ ለባሹ... በመስዑድ ሙስጠፋ
ክፍል -1
መቼም ብዙ ሰው እድር፤ የፖለቲካ ፓርቲ፤ ወታደር እና መስከረም 30 ምን እና ምን ናቸው ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ እንዴት ተገናኙ የሚልም አይጠፋም፡፡ በሁለት ክፍል ሃሳቤን አቀርባለሁ:: የመጀመርያው ክፍል መግብያ መሆኑ ነው፡፡
ትላንት ምሽት የጃዋር እና ልደቱን ውይይት ተመለከትኩ፡፡ ሁለቱም በዚህችሀገር ላይ የአደባባይ ሰዎች የሚባሉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የሚያራምዱት የፖለቲካ ርእዮት ፍጹም ተቃራኒ የሚባል አይነት ቢሆንም ትላንት ግን ሁለቱም በደንብ ተናበው አምሽተዋል፡፡ ጃዋር እንዳለው ሳይነጋገሩ በደንብ ተግባብተዋል፡፡ ይህ ተከሰተ የተባለው “ህገመንግስታዊ ቀውስ” ምን ያህል ለነልደቱ እና ጃዋር አይነት ፖለቲከኞች ፈጣን ወደስልጣን መምጫ ተደርጋ እንደታየች በንግግራቸው በድፍረት ከጠቀሱት ነገሮች ማየት ይቻላል፡፡ለነገሩ ፓለቲከኛም ፓርቲም እንደዚህ ለስልጣን ነው የምታገለው ብለው በግልጽ ሲናገሩ ለእውነቱ ይበልጥ የቀረቡ ይመስለኛል፡፡
እንደ መግብያ
በ2016 በፈረንጆች አቆጣጠር ጃዋር አሜሪካ ሃገር በቀድሞ አዲስ ነገር ጋዤጠኞች ትታተም በነበረው 7 ኪሎ ጋዜጣ “ዋናተኛው ጃዋር” በሚል ሰፊ ቃለመጠይቅ ሰጥቶ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እዴት አድርጎ ፖለቲካውን እንደሚቀዝፍ በዝርዝር የገለጸበት ቃለመጠይቅ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ጃዋር በርግጥም ጥሩ ዋናተኛ መሆኑን ትላንት ከልደቱ ጋር በመሆን አንተ ትብስ አንተ ትብስ ተባብለው ባመሹበት መድረክ ላይ በድጋሚ አረጋግጦኛል፡፡ ከ"oromo first" የጀመረው ትግል "Ethiopia out of Oromia" አድጎ ትላንት ምሽት ደግሞ "ጨቋኝዋን ኢትዮጵያንና የጋራ ታሪክ የሌለውን" የኢትዮጵያን ህዝብ ከ"ህገመንግስታዊ ቀውስ" እና እልቂት በ"ፖለቲካዊ መንገድ" ስለመታደግ ሲያስረዳን ነበር፡፡ ከዋኙ አይቀር እንደዚህ ነው፡፡
ትላንት ምሽት እንደ ህገመንግሰት አርቃቂዎቹ በሁለቱም በተደጋጋሚ መወድስ የቀረበለት የለም፡፡ “አንባገነናዊ ስርአት እንዳይፈጠር ፤ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ የስልጣን ጊዜን ማራዘም እንዳይቻል” ህገመንግስቱን በደንብ አስበውበት እንደጻፉት አብራርተዋል፡፡ ታድያ እነዚህ ባለብሩህ አርቃቂዎች አንድ ያደረጉት ነገር ህግ የመተርጎም ስልጣንን ለፌዴሬሽ ምክርቤት ቢሰጡም ትላንት ምሽት ልደቱ “ህገመንግስቱን ለመተርጎም ሕግ ማወቅ አይጠይቅም፤ ማንበብ እና መፃፍ ብቻ በቂ ነው” ብሎ ተሳልቆበታል፡፡ ይብላኝ ለተርጓሚዎች፡፡
መቼም አምልጦት መሆን አለበት እያልኩ ሳስብ ሌላ አስደማሚ ነገር ተናገረ ልደቱ "አብረን እንስራ ስንል ስልጣን አጋሩን ሳይሆን ሸክምና ሀላፊነትን እንጋራ ማለት ነው፤ ይህን የመሰለ ተቃዋሚ ማግኘት መታደል ነው"፡፡ ይህን የመሰለ ተቋዋሚ ማግኘት መታደል ነው የተባለላቸው ተቋዋሚዎች አብዛኛዎቹ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ 10ሺ የድጋፍ ፊርማ ማምጣት አንችልም ብለው በይፋ የተናገሩትን ወይስ ከሌላ ሃገር ልናስመጣ ነው? እረ ግራ አታጋቡን ወገን፡፡
ቆይ ቆይ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ ይቸግረናል ሲሉ የነበሩ ታድያ እንዴት በመቶ ሚልዮን ህዝብ ህልውና ላይ ለመወሰን የሞራል ብቃት አገኙ የሚለው ጥያቄ ለልደቱ ብቻ ነው የማያደናግረው ፡፡ ሰሞኑን ተከሰተ ከተባለው ህገመንግስታዊ ቀውስ ወዲህ እነዚህ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች- አንድ ወዳጄ የ”ሳምሶናይት ፓርቲዎች” -ቢላቸውም የሽግግር መንግሰት ምስረታ ውስጥ ስለሚደርሳቸው ሚንስትር መስርያ ቤት እያጤኑ መሆኑን በገደምዳሜ እነገሩን ነው፡፡
ትንሽ ቆይቼ ስለፓርቲዎች፤ የሰፈር እድሮች፤ መስከረም 30 እና ስለመለዮ ለባሹ እቀጥላለው፡፡














