ገና መሆኑን ያውቃሉን?
ድርቅ ርሃብ ጠኔ 2015/16
በኢትዮጵያ ከ1983-85 በተከሰተው ድርቅ የሚዲያ ዘገባ ተከትሎ በቦብ ጌልዶፍ አስተባባሪነት በሙዚቀኞች የተዘጋጀ ግብረ መልስ የሙዚቃ ኮንሰርት ነው “Do they know it’s Christmas?”. ነጠላ ዘፈኑ በአንድ ቀን እንደተዘጋጀና ሪከርድ ሰባሪ ተደማጭነት እንደነበረው ታሪክ ያስረዳል።። የእርዳታ ባንዱ/Band aid/ ለራሱ ከፍተኛ ከሕዝብ ጋር የማስተዋወቅ አገልግሎት ከማትረፉ በተጨማሪ ለሰብዓቂ ርዳት ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይዘነጋም። በዚህ ጦማር ስለ ሙዚቃው ፣ የቢቢሲ ዘገባና ሙዚቃው በኢትዮጵያ ዘላቂ ገጽታ ላይ ምን ያህል ጥላ እንዳሳረፉና ርዳታ ይጠቅማል/አይጠቅምም ክርክር ለመዳሰስስም አይሞክርም።
ኢትዮጵያና ተፈጥሮዋ
ብዙ ምሁራን ዛሬ ለምን ዓለማችንን የምዕራቡ ክፍል መምራት ቻለ የሚለውን ጉልህ ጥያቄ ሲመልሱ የሚጀምሩት ከጂኦግራፊ ነው። የሰው ልጅ አንዱን ለዘመናት ፍራፍሬ ለቃሚና አትክልት አዳኝ ብቻ ሌላውን የተሻለ ስልጡን ለማድረግ የወንዞች አወራረድ፣ የቀኑ ብርድና ሙቀት፣ ከውቅያኖስ ያላቸው ቅርበትና ርቀት፣ መሬት በውስጧ ቀብራ የያዘችው ማዕድን ወዘተ ጉልህ አስተዋኦ እንዳደረገ ብዙዎች ይስማማሉ። ፕርፌሰር ጌታቸው ሃይሌ የግዕዝ ብራና ድርሳናትን ጨምቀው ባቀረቡበት ጽሑፋቸው ድርቅ፣ ርሃብና ጠኔ በኢትዮጵያ ያልነበረበት ዘመን የለም ማለት ይቻላል ይላሉ።። በሳይንስ እጅግ ከባድ የአየር ጸባይ መናጋት ለፈጠራ ሰዎችን የመግፋት ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ቢታመንም ኢትዮጵያውያን ግን ከቦታ ቦታ ከመሰደድና እጃችንን ወደ ሰማይ ከመዘርጋት ያለፈ አንዳችም የተለየ የድርቅ መቋቋሚያ ስልት መፍጠር አልቻልንም። የእስራኤላውያንን ወደ ግብጽ በድርቅ የተነሳ ወደ ግብጽ መሰደድ ፣ የዮሴፍን የመጀመሪያው የድንገተኛ አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር መሆን፣ በዮሴፍ መሪነት በተጠራቀመ እህል አለም ከጥፋት እንደዳነ ሙሴን ሙሳ ፣ ዮሴፍን የሱፍ ብለው የሚተርኩ የድሮ ልሂቃን ካሀናትና ሼኮቻችን በሺህ ዘመን ለሚቆጠር ዘመናት ቢኖሩንም ጎተራ ሳይሰራ የመስኖ ውሃ ሳይጠለፍ ይሄው በ2015 ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰው ተርቦብን ርዳታ በመለመን ላይ እንገኛለን። ከላይ ሳውዲ አረቢያ የሚባል የነዳጅ ባለሃብት ከታች ደቡብ ሱዳን ተዛምደውን እኛ ብንቆፍር ሉሲንና ዘመዶቿን እንጅ ነዳጅ ሳይገኝ ይሄው አለን። ከዚህ በተጻራሪ ሁኔታ ለእርሻ እጅግ ተስማሚ የሆነ አየር ጸባይ (13 months of sunshine) ቢሰራባቸው ብዙ ሊያበሉ የሚችሉ ወንዞች ቢኖሩንም ለበሬና ገበሬ ገዳይ በሆነ ከሺህ ከዘመናት በፊት በተፈጠረ ኋላ ቀር አስተራረስ ስለምንጠቀም ስንዝር መራመድ አልቻልንም። ስለዚህ ተፈጥሮዋ ያለውን አልተጠቀምንበትም የሌለው ለፈጠራ አላተጋንም።
ኢትዮጵያና የአብርሃም አምላኳ
ለመካከለኛው ምስራቅ ቅርብ መሆኗን ተከትሎ አብርሃማዊ የምንላቸው ይሁዲ፣ክርስትናና እስልምና ከመላው ዓለም ቀድማ የተቀበለች ዛሬም ሳታስታጉል የአብርሃምን አምላክ ጆሮ በሚበሳ ማይክራፎን በቅዳሴና በአዛን ስሙን የምትጠራ ሀገር ናት። በቅርቡ pew research ባቀረበው “Importance of religion in people’s lives” 98% ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት በሕይወታቸው ወሳኝ እንደሆነ በመመለስ ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካም አንደኛ ሆነናል። ስሙ የተለያየ ይሁን እንጅ ሰፋ ባለ አንጽሮት ላስተዋለው የኢትዮጵያ አምላኳ አንድ የአብርሃም አምላክ ነው። ገና የክርስቲያኖች በዓል ቢሆንም እንደዛሬው መካረር ባልነበረበት ዘመን (ዛሬ ለስንዴና ዘይት ሃይማኖት ሳይለዩ የተሰለፉ ወገኖች) ለኢሳ ልደት በዓል ቢጠሩ ዳቦ አንበላም የሚል ሙስሊም ጥቂት ነው።
ገና በምዕራቡ ዓለም
ምዕራቡ ዓለም በባሕል የካቶሊካዊንት ቤተክርርስቲያን አቆጣጠርን የሚከተል ሃይማኖታዊ ባሕሏንም እንደዘመኑ እዬዋጀ የሚኖር ማህበረሰብ ነው። የክሪስማስ የፌሽታ ዘመን የሚጀምረው ከህዳር ቢሆንም ዋናው በዓሉ የታህሳስ መጨረሻ ሳምንት እና የአዲስ ዓመታቸው መጀመሪያ ጥር ቀዳሚ ሳምንት ማለት ይቻላል። በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ መደበኛ ስራ አይሰሩም። በዋናነት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ፣ ስጦታ በመሰጣጠት እና ፌሽታ በማድረግ ነው የሚያሳልፉት። በገና ወቅት ከሚገኝ ምቾት የተነሳ ሊቀለበስ የማይችል የሰውነት ክብደት መጨመር ሊከሰት ስለሚችል ሰው የአመጋገብ ስልቱን በጥንቃቄ እንዲከታተል የህክምና ባለሞያዎች ይመክራሉ።
Do they know it is Christmas?
የሙዚቃ ደራሲውን ስንኞች አንድ በአንድ እዬነቀሱ የሚተቹ ኢትዮጵያውያን ወግ አጥባቂ ምሁራን “ገና መሆኑን ያውቃሉ ወይ” የሚለውን ጥሬ ትርጉም በመያዝ አውሮፓ ሳይበራለት ክርስቲያን ነበርን፣ በራሳችን አቆጣጠር የምንጾም የምንፈስክ የገና ወቅት መሆኑን አሳምረን የምናውቅ ነን ሲሉ ዘራፍ ይላሉ። ደራሲው ግን እሚያወራው ፌሽታ፣ ስጦታ፣ ስኖው(አመዳይ)፣ብርሃን(የፈረንጆቹ ክረምት ስለሆነ ብርሃን ወጣ የሚለው የግሪክ አሊጎሪ ትርጉም ይሰጣል) እንዳጣንና የሚያቃጥል ፀሐይ ብቻ እንደቀረን ነው። የቢቢሲው ጋዜጤኛ ኮረምን “The nearest place to hell” ሲል ገልጿት ነበር። ወደ ገነት መግቢያዎቹ ላሊበላና ነጃሺ ለመድረስ ጥቂት ብቻ ወክ መብላት ይበቃው እንደነበር ጠፍቶት አይመስለኝም።የሚያሳዝነው የሚዲያ ዘገባውና የሙዚቃው ተጽዕኖ ዛሬ ድረስ የሚበላ ያለን የማይመስላቸው ሰዎችን ፈጠረ። እኛም የድንቁርናችን ክፋት ከ30 ዓመት በኋላ የተረጅ ቁጥር ጨምረን ለእርዳታ ተሰለፍን። የዘፈኑን ሊሪክስ ከዚህ ይገኛል
ኢና ሚን ሌማለት ተፈልጎ ነው?
ገና 2008ን ያለ ጥጋብ፣ ፌሽታ፣ ውሃ ያሳለፋችሁ ገና እንዳለፈ ጾመ ልጓሙ እንደተፈታ አውቃችኋልን? በድርቅና ጠኔ ለሚሰቃዩ ወገኖቼ፣ ቲቪና ተምብለር ለማያውቁት ወገኖቼ ገና ማለፉን ሰምታችኋልን ለማለት ፈልጌ ነው(ከህሊናዬ ይውጣልኝ እንጅ መልዕክቴ ባይደርሳችሁ ግድ አይሰጠኝም)። በደህና ጊዜ በታህሳስ ጎተራህን አብስ የዘመርነው አዲስ ምርት ሊገባ እንዳለ ታሳቢ አድርገን ነው። ዘንድሮ በታህሳስ ጎተራ አይታበስም። በጥርም ምርት አይበጠርም። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በዘልማድ ቅበላ የሚባለው የምርት መሰብሰብን ተከትሎ ሰርግ የመሰረግ ስነስርአትም አይኖርም።(ያው ሃይለ ስላሴ የልጃቸውን ልደት በኬክ እንዳከበሩት ሃይለ ማርያም ልጃቸውን ያለ ውስኪ ከመዳራቸው በስተቀር) (ጴንጤ አልኮል አይጠጣም ብዬ ነው) ። ቀንን የፀሐይን መግባትና መውጣት ተከትላችሁ የምትቆጥሩ የሀገሬ መናጢ ደሃዎች፣ የወቅቱን መፈራረቅ በዝናብ መዝነብ፣ በአበባው ማበብና ማሸት ብቻ የምታውቁት ወገኖቼ ገና እንዳለፍ አውቃችሁን? አዎ ሰንጋ ሳትጥሉ፣ የባቄላ፣ አተር እሸት ሳትቀምሱ፣ አሲና ገናዬ ሳትጫወቱ ገና አልፏል።
ማምለጫ ቅኔ:
1)ሥጋ እበላ ብዬ ገና በተመኘሁ፣ አሁን ከምን ግዜው ምላስ ገብቶ አገኘሁ
2) በገና በጥምቀት አልልህም ጠጅ፣ ኋላ በትንሣኤ አትበድለኝ እንጅ
k:$h,A&�ו�zn













